የቡና ግብይት ስርዓቱ ግልጽ አስተማማኝና ቀልጣፋ ነው ኣሉ



በሃዋሳ እና በሌሎች ከተሞች የተገነቡ የቡና ቅምሻና ጨረታ ማዕከላት የቡና ግብይት ስርዓቱ ላይ ይታይ የነበረውን ችግር በማስቀረት ግብይቱ ግልጽ አስተማማኝና ቀልጣፋ እንዲሆን ኣስችለዋል መባሉ ተሰምቷል፤ ከክልሉ በተያዘው ዓመት ከ134 ሺህ ቶን የሚበልጥ የታጠበና ደረቅ ቡና ለገበያ ይቀርባል እየተባለ ነው። ወሬው የኢዜኣ ነው፦
ከደቡብ ክልል ለገበያ የሚቀርበውን የቡና መጠን በጥራት በመጨመር የሀገሪቱን የውጪ ምንዛሪ ግኝት ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የክልሉ ግብይትና ህብረት ስራ ቢሮ አስታወቀ፡፡
በቢሮው የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች የስራ ሂደት ባለቤት አቶ መላኩ እንዳለ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ከክልሉ በተያዘው ዓመት ከ134 ሺህ ቶን የሚበልጥ የታጠበና ደረቅ ቡና ለገበያ ይቀርባል።
ክልሉ ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና ማምረት የሚችል ቢሆንም ህገወጥ የቡና ግብይትና ዝውውር በገበያው ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ለውጪ ምንዛሪ መጠን ማነስ ምክንያት ሆኖ መቆየቱን ጠቁመዋል።
ህገወጥ የቡና ዝውውርና ግብይትን ለማስቀረትና በግብይት ስርዓቱ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ለውጪ ገበያ የሚቀርበውን ቡና ጥራት ለማስጠበቅ የቡና ግብይት ደንብና መመሪያ ተዘጋጅቶ ግባራዊ መሆኑን ገልጸዋል።
የቡና ግብይት ስርዓቱ እሴት በማይጨምሩ ደላሎችና ህገወጥ የቡና አዘዋዋሪዎች እጅ የወደቀ በመሆኑ አምራቹ ለምርቱ ተመጣጣኝ ዋጋ እንደማያገኝ ገልጸው በቡናው ላይ የጥራት መጓደል ችግር የሚፈጠር በመሆኑ የሚፈለገውን ያህል ገቢ ማግኘት እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡
የቡና ግብይት ስርዓቱ ግልጽና የአምራቹን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንዲያስችል የገበያ መሰረተ ልማት የማስፋፋት ስራ መከናወኑን ገልጸው ባለፉት አራት ዓመታት አንድ ሺህ 618 የመጀመሪያ ደረጃ የቡና ግብይት ማዕከላት በማቋቋም ሕጋዊ ነጋዴዎች ፈቃድ በመያዝ እንዲሰሩ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
የመጀመሪያ ደረጃ የቡና ግብይት ማዕከላት ለአርሶ አደሩና ለግብይት ተሳታፊዎች ከሚሰጡት ጥቅም ባሻገር የቡና ጥራትን ለማስጠበቅና ህገወጥ የቡና ንግድና ዝውውርን ለመቆጣጠር አስችሏል ብለዋል፡፡
በሀዋሳ ፣ዲላ ፣ወላይታ ሶዶና ቦንጋ ከተሞች የተገነቡ የቡና ቅምሻና ጨረታ ማዕከላት ስራ በመጀመራቸው የቡና ግብይት ስርዓቱ ላይ ይታይ የነበረውን ችግር በማስቀረት ግብይቱ ግልጽ አስተማማኝና ቀልጣፋ እንዲሆን ማስቻሉን አስታውቀዋል፡፡
ከክልሉ በያዝነው አመት ለውጪ ገበያ የሚቀርበው የቡና መጠን ካለፈው አመት በመጨመር የውጪ ምንዛሪ መጠንን ለማሳደግ ለግብርና ባለሙያዎች አርሶ አደሮችና ለግብይት ስርዓቱ ተሳታፊ ለሆኑ አካላት ስልጠና መሰጠቱን ጠቁመዋል፡፡
በያዝነው አመት በማህበራትና በግል ለገበያ የሚቀርበው የታጠበና ደረቅ ቡና ካለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር ከ43 ሺህ ቶን በላይ ብልጫ እንዳለው አቶ መላኩ አስታውቀዋል፡፡
ምንጭ፦ ኢዜኣ

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር