ቦርዱ በአቶ ትዕግስቱ ለሚመራው የአንድነት ፓርቲ እና በአቶ አበባው ለሚመራው መኢአድ ፓርቲ ዕውቅና ሰጠ

አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2007 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ጽህፈት ቤት በአመራር ውዝግብ ውስጥ በነበሩት አንድነት ለፍትህ እና ለዴሞክራሲ ፓርቲና በመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ዙሪያ ውሳኔ አሳለፈ።
አንድነትን በተመለከተ አቶ ትዕግስቱ አወሎ የፓርቲው ህጋዊ ሊቀመንበር ናቸው ብሏል።
በመኢአድ በኩል ለአቶ አበባው መሃሪ የፓርቲው የህጋዊ ፕሬዚዳንትነት ዕውቅናም ሰጥቷል።
አንድነትም ሆነ መኢአድ ቦርዱ ዕውቅና በሰጣቸው መሪዎች እየተመሩ በምርጫው መሳተፍ እንደሚችሉም ነው የተወሰነው።
መግለጫውን የሰጡት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ፀሃፊ አቶ ነጋ ዱፌሳ ቦርዱ ለሁለት የተከፈሉትን የሁለቱንም ፓርቲዎች አመራር ችግራቸውን ለመፍታት የተሰጣቸውን ጊዜ ለመጠቀም ያከናወኗቸውን ተግባራት በጥልቀት መመርመሩንም ተናግረዋል።
ቀደም ሲል የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አንድነትና መኢአድ በውስጣቸው የተከሰተውን ችግር ፈትተው እንዲመጡ የ14 ቀናት ጊዜ ሰጥቶ የነበር ሲሆን፥ ቦርዱ የጊዜውን መጠናቀቅ ተከትሎ በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት የመጨረሻ ውሳኔ ለማሳለፍ በዛሬው ዕለት ቀጠሮ መያዙ ይታወሳል።
በአቶ በላይ ፈቃዱ የሚመራው አንድነት የምወያየውም ሆነ የማካሂደው ጠቅላላ ጉባኤ የለም በማለት ባለፈው አርብ በሰጠው መግለጫ ሲያስታወቅ፣ በአቶ ትዕግስቱ አወሉ የሚመራው የአንድነት ቡድን ደግሞ ቅዳሜ እለት ባካሄደው ጉባኤ ፕሬዝዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንቱን ጨምሮ ሌሎች አመራሮቹን መምረጡም አይዘነጋም።


Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር