በአቶ ሌንጮ ለታ የሚመራው የኦዴግ ልዑካን መንግሥት ሊያነጋግረው ባለመቻሉ መመለሱን ገለጸ

በአቶ ሌንጮ ለታ የሚመራው የኦዴግ ልዑካን መንግሥት ሊያነጋግረው ባለመቻሉ መመለሱን ገለጸ

‹‹አዲስ አበባ ገብተው እንደነበር አላውቅም›› አቶ ሽመልስ ከማል
ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የተቋረጠውን ድርድር ለማስጀመር መጋቢት 9 ቀን 2007 ዓ.ም.  አዲስ አበባ እንደገባ የሚገልጸው በቀድሞው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀመንበር የሚመራው፣ የአሁኑ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) ልዑካን ቡድን ከመንግሥት ወገን የሚያነጋግረው በማጣቱ ወደ ካናዳ መመለሱን ገለጸ፡፡
የኦዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መጋቢት 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ከመንግሥትና ከገዥው ፓርቲ ኃላፊዎች ጋር በስልክ ከመነጋገር ባለፈ በአካል መገናኘት ባለመቻሉ ማዘኑን ገልጿል፡፡ ነገር ግን ወደ ተነሳበት ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ከመጓዝ ተስፋ እንደማያስቆርጠው አስገንዝቧል፡፡ 
በተለያዩ የማኅበራዊ ድረ ገጾችና የተለያዩ ጦማሮች መንግሥት አቶ ሌንጮ ለታንና የልዑካን ቡድኑን አባላት ከቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት እንደመለሳቸው ሲናፈስ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ግንባሩ ባወጣው መግለጫ ከፍተኛ የልዑካን ቡድኑ አዲስ አበባ ከገባ በኋላ፣ በአዲስ አበባ ቆይታው ከመንግሥት ኃላፊዎች ጋር በአካል መገናኘት ባለመቻሉ መጋቢት 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ወደ ካናዳ መመለሱን ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ከኦዴግ ጋር እንዲደራደር ለማሳመን ለሁለት ዓመት ግንባሩ ከውጭ በመሆን ጥረት ሲደረግ መቆየቱን፣ በስተመጨረሻም በግንባሩ ውሳኔ ፕሬዚዳንቱ አቶ ሌንጮ ለታ የሚመሩት የልዑካን ቡድን ወደ አዲስ አበባ እንዲጓዝ መደረጉን ይገልጻል፡፡ ኦዴግ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል በማድረግ የኦሮሞ ሕዝብ መብትና ነፃነት የማስከበር፣ እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲና ብልፅግናን ለማቀዳጀት እንደሚሠራ አስታውቋል፡፡ 
ይህንንም ዕውን ለማድረግ ከአገር ውጭ ሆኖ ሳይሆን፣ በኦሮሞ ሕዝብ መካከል ሆኖ በሕግ አግባብ ተመዝግቦ ፖለቲካዊ ትግል ለማድረግ መወሰኑን መግለጫው ያስረዳል፡፡ በዚህ የግንባሩ መርህ መሠረት መንግሥትንና ሌሎች ፖለቲካ ፓርቲዎችን በተለይም ገዥው ፓርቲን ኢሕአዴግን ወደ ድርድር ለማምጣትና መሠረታዊ ልዩነቶችን ለማስታረቅ፣ እንዲሁም ግንባሩ በኢትዮጵያ መቀመጫውን እንዲያደርግ ሰፊ ጥረት ቢደረግም ሊሳካ አለመቻሉን መግለጫው ያትታል፡፡ 
‹‹በአዲስ አበባ ከመንግሥት ኃላፊዎች ጋር ተገናኝተን ድርድር አለመጀመራችን ተስፋ የሚያስቆርጠን ሳይሆን፣ ድርጅታችንን በሕዝባችን መካከል ለመመሥረት የምናደርገው ጥረት መጀመርያ ነው፤›› ይላል መግለጫው፡፡
ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ያለውን አቋም በድጋሚ የገለጸው ግንባሩ፣ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ፖለቲካ ተዋናዮች በተለይም ገዥው ፓርቲና ዓለም አቀፍ ደጋፊዎቹ የግንባሩን ጥረት በመልካም ጎኑ እንዲቀበሉ ጥሪ አቅርቧል፡፡ ጉዳዩን በተመለከተ የተጠየቁት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማል፣ አቶ ሌንጮና የልዑካን ቡድኑ አዲስ አበባ እንደነበሩ አላውቅም ብለዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር