የንግሥት ፉራ አፈታሪክ

የንግሥት ፉራ አፈታሪክምንጭ፦  ሪፖርተር
በሲዳማ ውስጥ አንዲት ስመ ገናና እና ታላቅ ንግሥት ነበረች፡፡ ይች ታላቅና ስመ ገናና ንግሥት የወንዶችን የበላይነት ሥርዓት አስወግዳ የሴቶችን የበላይነት ለመመሥረት ጥረት ያደረገች ስትሆን በጀግንነቷ ወደር እንዳልነበራት ይነገርላታል፡፡
ሆኖም ስለዚች ታላቅ ንግሥት ትኩረት የተሰጠው ካለፉት አሥር እና አሥራ አምስት ዓመታት ወዲህ ነው፡፡ በዚህ ረገድ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በሲዳማ ዞን መጠነኛ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በትውልድ ስፍራዋ በይርጋለም የምርምር ተቋም በስሟ ተቋቁሟል፡፡ በሐዋሳ ውስጥም አደባባይና የጉባኤ አዳራሹ እርሷን ለማስታወስ በሚያስችል መልኩ ተቋቁመዋል፡፡ ሆኖም ስለዚህ ታላቅ ንግሥት የምናገኛቸው የሥነጽሑፍ ሥራዎች ውሱን ናቸው፡፡ 
ስለሆነም ወጣቱ ትውልድ ንግሥት ፉራንና ሌሎችም በአፈታሪክ የምናውቃቸው የአገራችንን ታላላቅ ሴቶች የበለጠ እንዲያጠና በማሰብ ይህ ጽሑፍ ተዘጋጅቷል፡፡
 የንግሥት ፉራን አፈታሪክ ስንመለከተው በጣም ትልቅ ነገር ግን የማይታወቅ ድንቅ ለልብ ወለድ፣ ለድራማ፣ ለፊልምና ለሌሎችም የሥነ ጽሑፍ ሥራ¬ዎ‹ የሚጠቅም ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ 
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የንግሥት ፉራ አፈ ታሪክ እንደትልቅ ባህላዊ ሀብትና እሴት ባለመቆጠሩ ምክንያት በተለይም ያለፈው አንድ ትውልድ ይህችን ንግሥት በከፋ ሁኔታ ረስቷት፣ ወይም እርባና ቢስ ተረት ነው በሚል አስተሳሰብ ትቷት ነበር፡፡ ይህም ሆኖ ታሪኳ በጣም ጠንካራ በመሆኑ ምክንያት አልፎ አልፎም ቢሆን በመገኛኛ ብዙኃን ብቅ ማለቷ አልቀረም፡፡ 
ጸሐፊው ከ1970-1976 በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሕፃናትና የወጣቶች ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢ ሆኖ ሲሠራ የሲዳማ ወጣቶች ኪነት ቡድን አባል ሆኖ የተዋወቀው አብርሃም ረታ ዓለሙ «ኦሶ ሀዬ ሃዬ» ሲጫወት የተቀረጸውና የተላለፈው ዘፈኑ ከንግሥት ፉራ ጋር የተያያዘ መሆኑን ተረድቷል፡፡ 
ስለርሷ ከሁሉም ምንጮች የተገኘው መረጃ በመጠኑ ይለይይ እንጅ በአመዛኙ ተመሳሳይ ነው፡፡ በ1981 ዓ.ም. በየካቲት መጽሔት ላይ ከሰፈረው ውስጥ በ15ኛውና በ16ኛው ክፍል ዘመን ወደ ሲዳሞ የፈለሰው የሲዳማ ብሔረሰብ አምባገነን ባላባት የነበረውን ባሏን ዲንጋሞ ኮያን በኮሶ መድኃኒት ሰበብ በመግደል ሥልጣን እንደያዘች ይገልጽና የገደለችውም በዘመዶቿ ላይ በደል ሲፈጽም ስለነበር ነው፡፡ በሱ ምክንያትም ወንዶችን ጠላች፡፡ በዚህ መጽሔት ጽሑፍ መሠረት ንግሥት ፉራ የጡማ፣ የሆሎ፣ የማልጋ፣ የሀዲቾ (ደራዋታ)፣ የሳያላ፣ የአለታ፣ የሐዊላ (ቂዊላ)፣ ጎሳ¬ዎች መሪ ነበረች፡፡ 
በተገኙት መረጃዎች መሠረት፣ ንግሥት ፉራ በ10ኛው ወይም በ16ኛው ክፍለ ዘመን የነበረች የሲዳማ ብሔረሰብ አባል ነበረች፡፡ ጎሳዋን በተመለከተ አቶ ስለሺ ወርቅነህ «አንዳንዱ መልጋ ናት ሲላት ሌሎች ደግሞ ሐቤላ/ሐዌላ ናት ይሏታል» በማለት አቋም ሳይወስዱ ይናገራሉ፡፡ አቶ ስለሺ በ16ኛው ክፍለ ዘመን ኖረች እንደሚባልም ያስረዳሉ፡፡
ሁለቱም እንዲያ ይበሉ እንጅ «የፉራ ጎሳ ጉዳይ ሲነሳ፣ የኔ እንጅ የናንተ አይደለችም» ከሚልም አስተሳሰብ የሚጠነሰስ በጎና በጎ ያልሆነ አስተሳሰብ ሊመነጭ ስለሚችል ነገሩን ሰፋ አድርገን ብንመለከተው መልካም ይመስላM:: 
በዚህ ጸሐፊ ግምት ደግሞ፣ የሲዳማ ሕዝብ ከአካባቢው ሕዝብ ጋር አብሮ የሚኖር ከመሆኑም በላይ የታላላቅ ጎሳዎች መሪዎች ከሌሎች ጎሳዎች አባላት ጋር የሚጋቡ ስለሆነ ቢያንስ የአራት፣ አምስትና ከዚያም የበለጠ የጎሳ¬ ዝርያ¬ዎ‹ አባል ሊኖራት ይችላል፡፡ ይህም ባይሆን ሰው በባሕሪው ዘሩን ከትልቅ ሰው ጋር ማያያዝ ስለሚወድ «ከኔ ጎሳ ናት» ብሎ ቢነሣ የሚገርም አይደለም፡፡ በዚህ ረገድ የሰለሞንና የዛጉዌ ዝርያ¬ች ነን፡፡ እንዲሁም የጀበርቲና የአባድር ዝርያ¬ች ነን የሚሉትን ሙስሊሞች በዚህ ረገድ ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ስለሆነም ሲዳማዎ¬ችም የዚች ዝነኛ መሪ ጎሳ አባል ለመሆን በመሻት አንዱ መልጋ፣ ሌላው ሐቤላ ወይም ኩሄሳ ቢላት ከሌሎች የተለየ አያደርገውም፡፡
በአፈታሪኩ የሚነሳው ሌላው መላምት ንግሥት ፉራም እንደ ንግሥት ዮዲት በዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ከኖረች ሁለቱ አንድ ይሆኑ ይሆን? የሚል ነው፡፡ በሐረር፣ በስልጤና በሌሎቹ አካባቢ¬ዎች የተለያየ ስም እንዳለት ይነገራልና፡፡ ያም ሆኖ ከማዕከላዊ መንግሥቷ ርቆ በሚገኘው አካባቢ ስሟ ሲረሳ በሲዳማና በአካባቢው ግን እስከ ዛሬ ሲታወስ መኖሩን በማንሳትም «የዛሬው ሲዳማና አካባቢው ሕዝብ ንግሥት ነበረች» የሚል ተጨማሪ መላምት መምታት ይቻላል፡፡ 
ዋናው ቁም ነገር በአፈታሪኩ መሠረት ፉራ የምትባል የሲዳማ/የደቡብ ኢትዮጵያ ንግሥት ነበረች፡፡ ይህችም ንግሥት ጦረኛ፣ አዳኝና ነገረ ጥበብ አዋቂ ስትሆን የሴቶችን የበላይነት አንግሣ ነበር፡፡ የአገዛዝ ዘመኗም «ለሴቶች የበላይነት የቆመ ነበር» ቢባልም በጥቅሉ ስንመለከተው ግን ለምክር ቅድሚያ የሚሰጥ ነበር፡፡ ለምሳሌ ሴቶች ባሎቻቸው በጥፋተኛነትና በአባካኝት እንዳይፈርጇቸው «ለባል የጥጥ ንድፍሽን፣ የጎመንና የበርበሬ ዛላ ቅንጥስሽን አታሳይው፣ ካየ የተነደፈው ጥጥ ብዙ፣ የተፈተለው ልቃቂት ትንሽ፤ የታደረግሽው? የጎመንና የበርበሬ ቅንጥስሽ ብዙ ያቀረብሽው ግን ትንሽ፣ የት አደረስሺው? ብሎ እንዳያስጨንቅሽ አታሳይው፤» የሚለው ይገኝበታል፡፡ ይህም የሚያመለክተው ፉራ በአጠቃላይ በወንዶች ላይ የተነሳች አረመኔ ፍጡር ሳትሆን ከቅጣት ይልቅ ምክርን የምታስቀድም ሰው የነበረች መሆኗን ነው፡፡
ንግሥት ፉራ የሴቶችን አምባገነን መንግሥት አስፍና እንደኖረች የሚያወሳ አፈታሪክ ቢኖራትም በሁሉም ወንዶች ላይም ቢሆን ለቅጣት የወረደች ፍጡር አለመሆኗን የሚያመለክቱ ሌሎች መረጃ¬ችም አሉ፡፡ ከነዚህም መካከል «ከሴቶች እንበልጣለን፣ እኛም እናወቃለን፣ እንችላለን ካላችሁ እኔ ሴቷ የምጠይቃችሁን ሁሉ መልሱልኝ፡፡ ካልመለሳችሁ የሚያውቁ ሴቶች መኖራቸውን እመኑ፣ ካላመናችሁ አርፋችሁ ተቀመጡ፣ ካልተቀመጣችሁ ደግሞ እርምጃ እወስዳለሁ፤» የምትል መሆኗ የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ ስለሆነም የሚያስቸግሯትን እየጠራች ከባድ ፈተና ጥያቄ ትጠይቅና የሚያረካትን መልስ ከሰጧት ምሕረት ታደርግላቸው ነበር፡፡ ለምሳሌ «የአንድ ቀን ሙሉ ጉዞ ከሚጠይቅ ቦታ ትኩስ የታለበ ወተት አምጡልኝ፡፡ በአየር ላይ ቤተ መንግሥቴን ሥሩልኝ» ብላቸው ትዕዛዟን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ስለመለሱ ምራቸዋለች፡፡ 
በእርግጥም በንጹህ ሕሊና ተነስተን «ይህ ለምን ሆነ?» ብለን ስንጠይቅ ወንዶች የበላይነታቸውን ለማሳየት የማይፈጽሙት አልነበረም፡፡ ለምሳሌ ሴቶች ወተት አልበው አርግተውና ገፍተው ቅቤ እያወጡ ወተቱን ቢጠጡትና ቅቤውን እንደልባቸው ቢቀቡት ወይም ቢበሉት እንደነውር ይቆጠርባቸዋል፡፡ ወንዶች ግን በአምስት ጣቶቻቸው እየዛቁ ይቀባሉ፡፡ ከምግባቸው ጋርም እየተደረገ ቢበሉት ነውር አይደለም፡፡ ይልቁንም አንዲት ሴት መቀባት ካማራት በትንሽ ጣቷ ጠንቁላ መቀባት፣ መብላት ካማራት ላመል ያህል አስነክታ መቅመስ፣ የአገሩ ልምድ ያስገድዳት ነበር፡፡ ስለሆነም ፉራ ለውጥ የማምጣት የቀን ሕልሟን እውን ለማድረግ ሴቶች በአምስት ጣታቸው ዝቀው እንዲቀቡ፣ ለወንዶች ግን በትንሽ ጣታቸው ጠንቁለው ግንባራቸውን እንዲያስነኩ አደረገች፡፡ ይህም ቀጭን ትዕዛዝ ሆነና «ሴቶች እንዲደሰቱ፣ ወንዶች ደግሞ እንዲከፉ አደረገች፤» ተባለ፡፡  
ይህም ንግሥት ፉራ በወንዶች ላይ በሴቶች ከፍተኛ ጭቆና ምክንያት ተነሳስታ በመጀመሪያ ነገሮችን ለማስተካከልና የሴቶችን ሰብአዊ መብት ለማስከበር ሞከረች፡፡ አልስተካከል ያሉትንና የሴቶችን ሰብአዊ መብት አንቀበልም ያሉትንም ለመምከር ሞከረች፡፡ ዳሩ ግን በሴት አንመራም ያሉ በልዩ ልዩ መንገድ የሚገለጹ አንዳንድ ሽማግሌ¬ዎች (የአካባቢ ሽማግሌ¬ዎች/ ጠንቋዮች) እና የነሱን አመለካከት የሚጋሩ ወንዶች መሰናክሎችን ስለደቀኑባት ከቀላል እስከ ከባድ እርምጃ መውሰድ ጀመረች፡፡
 ከወሰደቻቸው ዕርምጃ¬ዎች መካከልም ወንዶች ሴቶች የሚያዟቸውን ተግባር እንዲያከናውኑ እንዲሁም የማይቻል ነገር እንዲሠሩ፣ ቅጣቱ ኃይለኛ ሲሆን ደግሞ እንዲገደሉ ታደርግ ነበር፡፡ ይህም ባህርይ በወንዶችም የሚታይ ሲሆን በአገራችን ለዚህ ዓይነተኛ የቅርብ ምሳሌ የሚሆኑን አፄ ቴዎ¬ድሮስ ናቸው፡፡ ፈረንሳዊው ናፖሊዮን ሁለት ጊዜ ተወዷል፣ ሁለት ጊዜ ተጠልቷል፡፡ ሞንጎሊያዊው ጀንጂስካን፣ የሀኑ አቲላ በአንድ በኩል ሲወደስ በሌላው በኩል ደግሞ ሲተች ኖረዋል፡፡ የዓለም መሪዎ¬ች ስምም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡
ይህም ሆኖ፣ የስልጣኗ ተቀናቃኞችና ጀሌ¬ዎቻቸው «ለሴት አንገዛም» ብለው እርሷን የሚያጠፉበት መንገድ መፈለግና ማፈላለግ ጀመሩ፡፡ በዚህ ሒደት ላይ እያሉም አንድ ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ ይኸውም የጀግኖች ጀግና መሆኗን ለማሳየት «ማንም ሰው ጋልቦበት የማያውቅ እንስሳ አምጡልኝና ልጋልብበት» ስትላቸው ቆርኬ አመጡላት፡፡ ቆርኪዋን ዲከቻ በተባለ ሐረግ አጠመዱና ከቤተ መንግሥቷ ግቢ አስገቡላት፡፡ እንዳታመልጥም እግሯንም፣ እጇንም፣ አንገቷንም፣ በረጅም ጠፍር አሠሩና እቤተመንግሥቷ ጓሮ አሠሩላት፡፡ በሩንም ግጥም አድርገው ዘጉት፡፡ ከዚያም «ምንም እንኳ ንግሥታችን ከሰማይ በታች የሚያስቸግርሽ ነገር ባይኖርም ለጥንቃቄው ያህል እንዲህ እንደያዝንልሽ መጋለብ ትችያለሽ፣ እንዳትጥልሽም በርጥብ ጠፍር ግጥም አድርገሽ እናስርሻለን፡፡ ወጥታ አደጋ እንዳታመጣም በሩን ግጥም አድርገን ዘግተነዋል፤» አሏት፡፡ አገላለጻቸውና አቀራረባቸው አስተማማኝ ስለነበረም ፈቃደኛ ትሆናለች፡፡ በተፈጥሮዋ ፈሪ ባትሆንም በዚህ ሁኔታ ፍርሃት ብታሳይ ትዋረዳለች፡፡ ስለዚህም ጀግንነቷን እስከ መጨረሻ ለማሳየት ፈቃደኛ ትሆናለች፡፡ ፈቃደኛ ሆናላቸው ቆርኬው ላይ ስትወጣም ከወገቧ በታች ያለውን አካሏን ግጥም አድረገው ያስሩላታል፡፡ ከዚያም  አጥብቀው የያዟት ለማስመሰል ሞከሩ አልቻልናትም፣ አስቸገረችን' አንቺም ሥራሽ ያውጣሽ ብለው ለቀቋት፡፡ ቆርኪዋም ደንብራ አጥሩን ጥሳ አመለጠች፡፡ የተሸከመችው ባዕድ ነገር አስደንብሯትም ጫካ ለጫካ ሮጠች፡፡ በዚህ ሒደትም የፉራ አካM ተቆራርጦ በየቦታው ወደቀ፡፡ ዛሬ ቦታው  በእጆቿ፣ በዳሌዋ፣ በጨጓራዋ፣ በገበናዋ፣ በሌሎችም አካላቷ ቦታ ይጠራል፡፡ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ ለቆየው የኢትዮጵያ አፈ ታሪክ ታሪክ ምስጋና ይግባውና በአንዱ ወይም በሌላው መልኩ ቀጥሎ እዚህ ደርሷል፡፡ ዳሩ ግን ይህ እጅግ ከፍተኛ የሆነ በመጀመሪያ የሲዳማ፣ ቀጥሎ የኢትዮጵና የዓለም የባህል ቅርስ መሆኑን ተገንዝቦ ልዩ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ 
በዚህ አጋጣሚ ከፉራ ጋራ ዲንጋሞ መኮያ የሚባል ጦረኛ የሚወሳ ሲሆን፣ ይህም ሰው በአንድ በኩል ባሏ ነው ሲባል በሌላ በኩል ከሷ በፊት የነበረ ጨካኝ መሪ ነበር ይላሉ፡፡ ይህንንም ታላቅ የጦር መሪ ፉራ መጠኑ በበዛ የኮሶ መድኃኒት ገድላዋለች ይላሉ፡፡ ከዲንጋሞ ኮያ ጋር ጎለልቻ አርዴ የሚባል ኃይለኛ መሪ ሲኖር ይህን የጦር መሪም ከፉራ ጋር ለማገናኘት እንደሚሞከር እናስተውላለን፡፡ ዋናው ቁም ነገር ሲዳማ እነዚህ ትልልቅ የጦር መሪ¬ዎ‹ የነበረች ከመሆኑም በላይ እነዚህን ጀግኖች ድል በማድረግ ወይም በመከላከል ህልውናዋን አስጠብቃ ስለመቆየቷ አንዳች ነገር የሚፈነጥቅ ነው፡፡ 
ያም ሆነ ይህ በሲዳማ ውስጥ የዲንጋሞ ኮያና የጎለልቻ አርዴ አፈታሪኮች በሲዳማ ሕዝብ ዘንድ ልዩ ስፍራ እንዳላቸው በዚህ አጋጣሚ መጠቆም አስፈላጊ ነው፡፡ ስለሆነም እነዚህ አይረሴ ታላላቅ የሲዳማ ጀግኖች እነማን ናቸው? ብሎ በዝርዝር ማጥናት አስፈላጊ ነው፡፡
ንግሥት ፉራን በሚመለከት ግን ሴቶች በመልካም አርአያነት ሲያከብሯትና ወደ መቃብሯ በመሄድ ቅቤ፣ ወተት፣ ጥራጥሬና ፍርፋሪ «ይህ ያንቺ ድርሻ ነው» በማለት ካለቸው ቆንጥረው ሲያካፍሏት (መሥዋዕት ሲያቀርቡ)፣ በአንዳንድ ሴቶች ላይም ዛር ወይም አቴቴ ሆና ትመጣ ነበር፡፡ ወንዶች ደግሞ እንደመጥፎ መሪ በመቁጠር ይረግሟታል፡፡ መቃብሯ አጠገብ ሲደርሱም ከሴቶች በተቃራኒ «አንቺስ አንድ ጊዜ ሳይሆን ደጋግመሽ ሙቺ» እያሉ በትራቸውን እንደጦር በመስበቅ ዓይነት እየቃጡ ያልፋሉ፡፡
ዳሩ ግን፣ ንግሥት ፉራ ጦረኛ ናት ሲባል ምን ማለት ነው? የፈረስ ጉግሥ፣ ጦር ውርወራ፣ ቀስት ማስፈንጠር ችሎታውን፣ መቼ፣ ከማንና እንዴት ተማረችው? ነገረ ጥበብ ከሸንጎ ሌላ ማወቂያ መንገድ ይኖራት ይሆን? ለምን በጠንቋዮችና በአንዳንድ ሽማግሌ¬ች ላይ ክንዷን ዘረጋች፣ የወንዶችን አምባገነን ሥርዓት አስወግዳስ ለምን የሴቶችን አምባገነን አገዛዝ ለመመሥረት ፈለገች? ግዛቷን እስከ የት ድረስ አስፋፋች? ብልህ ነበረች ሲባልስ እንዴት ይገለጣል? 
ከሕፃንነቷ ጀምሮ ብልህ እንደነበረች የሚያወሳው መረጃ እንደሚያመለክተው በእርሷ ዘመን ወይም ቀደም ብሎ የነበረው ንጉሥ የነበረው ለሕዝቡ እንቆቅልሽ ሲሰጥ እሷ ከሁሉም በልጣ መልሱን በቀላሉ ትሰጥ ነበር፡፡ ለምሳሌ፡-
ሀ- የንጉሡ እንቆቅልሽ
ንጉሡ ከሰጣቸው እንቆቅልሾቹ መካከልም «የእናቴን በሕይወት መኖሯን ወይም አለመኖሯን ሳትገልጡ ዜናዋን ላኩልኝ» በማለት በእናቱ አገር ለሚኖሩ ሰዎ¬ች ላከባቸው፡፡ እነሱም የሚኖሩት ፉራ በምትኖርበት መንደር ነበር፡፡ የሀገር ሽማግሌ¬ዎች የንጉሡ እንቆቅልሽ እንዴት እንደሚፈቱ ተሰብስበው መመካከር ጀመሩ፡፡ ዳሩ ግን «እናትህ ደኅና ናት» እንዳይሉት፡፡ «በሕይወት መኖሯን ገልጻችኋል»፤ «ሞታለች» እንዳይሉትም መሞቷን እንዳትነግሩኝ በማለት ስለከለከላቸው ይቀጣቸዋል፡፡ ስለዚህ ምን መባል እንዳለበት ለማወቅ መረጃ ሲያሰባስቡ ሰነበቱ፡፡ እንደሚባለው ከሆነ ምሥጢሩን ለማወቅ ያላረጉት ጥረት የለም፡፡ በመጨረሻም አንዲት ሕፃን ልጅ በዚህ እንቆቅልሽ መጨነቃቸውን ተረድታ «በሉ እንዲህ አድርጉ፡፡ ጸጉራችሁን በግማሽ ተላጭታችሁ ሂዱና እጅ ነስታችሁ እፊት ለፊቱ ቁሙ፡፡ ካልጠየቃችሁ በስተቀር እንዳትናገሩ፡፡ ሲጠይቃችሁ ግን እንዲህ በሉት» በማለት እንቆቅልሹን በእንቆቅልሽ እንዲመልሱ መከረቻቸው፡፡ ሰ¬ዎቹም ከንጉሡ ቤተ መንግሥት እንደደረሱ  ለአጋፋሪው የእቆቅልሹን መልስ ይዘው እንደመጡ ገልጠው እንዲያስገባቸው ጠየቁት፡፡ አጋፋሪውም ወደ ንጉሡ ሄዶ የእናቱ አገር ሽማግሌዎች የእንቆቅልሽ መልስ ይዘው መምጣታቸውን ነገረው፡፡  
ንጉሡ ፈቅዶላቸው እንደገቡም የራሳቸውን ክንንብ አውርደው እፊቱ ቆሙ፡፡ የራሳቸውንና የጺማቸውን ግማሽ ጎን የተላጩት ያገሩ ሽማግሌ¬ዎች ያየው ንጉሥም በሁኔታው በመደነቅ «ምነው እናቴ ምንሆነች?» በማለት ጠየቀ፡፡
የሽማግሌ¬ዎቹ መሪም «ምን የርሷ ነገር» አሉና ዝም አለ፡፡
ንጉሡም «ሞተች እንዴ?» ብሎ ሲጠይቅ
«ብትሞት ኖሮ ጸጉራችንን እናሳድግ ነበር?»
«እና በሕይወት አለች ማለት ነው?» አለ ንጉሡ፡፡
እነሱም «በሕይወት ብትኖር እንደዚህ ጸጉራችንን እንላጭ ነበር?» በማለት መለሱ፡፡
በዚህ ጊዜ ንጉሡ እንቆቅልሹ በእንቆቅልሽ መመለሱን በማወቅ ከፍተኛ ድምፅ አሰምቶ ሳቀና «ከፍተኛ ጠንቋይ ወይም ሽማግሌ መሆን አለበት፡፡ እንዴት ያለ ብልህ ሰው መከራችሁ?» በማለት ጠየቃቸው፡፡ 
እነሱም ከመጫወት በስተቀር ሌላ ምንም የማታውቅ ሕፃን መሆኗን ነገሩት፡፡ ንጉሡም «ይች ስታድግ አገር የምትመራ ናት» ብሎ ተናገረ፡፡
ለ- ያለዕቃ ዕምቧይ ጭናችሁ አምጡ
ንጉሡ በመቀጠልም ሕዝቡን ሰበሰበና «አንድ ሺሕ እምቧይ ያለ ስልቻ ወይም ቁና፣ ወይም ገበቴ በአህያ ጭናችሁ አምጡልኝ ይላል፡፡ ሰ¬ዎ‹ እንዴት አድርገው ያለ መያዣ እንደሚጭኑ ማወቅ ተስኗቸው ሲጨነቁ ሕፃኗ ፉራ ትሰማለች፡፡ በዚህ ጊዜ «ለምን በቀላሉ ነገር ትጨነቃላችሁ እኔ እንኳን እጫወትበታለሁ» ካለች በኋላ «በመጀመሪያ አህያ¬ቹን ወይም በቅሎ¬ቹን አዘጋጁ፡፡ ከዚያም በእያንዳንዱ እንስሳ ላይ ጭቃ አድርጉበትና እጭቃው ላይም እምቧዩን ሰኩበት» በማለት መከረቻቸው፡፡ እነሱም ባገኙት ምክር መሠረት በብዙ አጋስሶች ወሰዱለት፡፡ ንጉሡ እንዳለፈው ጊዜ ሁሉ  ማን እንደመከራቸው ሲጠይቁ ያችው ሕፃን መሆኗን አስረዱት፡፡ እሱም «እንዲህ ያለች ብልህ ለቤተ መንግሥቱ አስፈላጊ ናት፤» አለና ሕፃኗን አሳድጎ ሊያገባት እንደሚፈልግ በመግለጽ ወደ አባቷ ሽማግሌ ተልኮ እንዲጠየቅ ሽማግለ¬ቹን አዘዛቸው፡፡ 
ሐ- የሴትና የምንቸት ትንሽ የለውም
ሽማግሌ¬ዎች ወደ አባቷ ሄደው ንጉሡ ፉራን ሊያገባት እንደሚፈልግ ገልጠው ፈቃደኛነታቸውን ይጠይቃሉ፡፡ አባቷም ልጃቸው ሕፃን እንደሆነች ገልጸው ጥያቄውን እንደማይቀበሉት ያስታውቃሉ፡፡ የመጡበት አገር ሩቅ ስለሆነም ምግብ እንዲመገቡ ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ጊዜ  ሕፃኗ ፉራ ወደ ጓሮ ትሔድና በትልቅ ቁና ሙሉ ጎመን ታመጣለች፡፡ ወዲያውም ተጥዶ ከነበረው ትንሽ ምንቸት ውስጥ ልታስገባ ስትሞክር አባቷ ያያሉ፡፡ በዚህ ጊዜ አባቷ «አየ የልጅ ነገር ይህንን ሁሉ ጎመን እዚያች ምንቸት ውስጥ?! በይ ተይው እናትሽ እትልቁ ምንቸት ላይ ታበስለዋለች» ይሏታል፡፡ ሽማግሌ-ቹም አብረው ይስቃሉ፡፡ 
ቀድሞውኑ ተዘጋጅታበት የነበረችው ፉራ ግን «አየ አባዬ! የሴትና የድስት ትንሽ አለ ብለህ ነው? ግድ የለም ለማየት ያብቃህ እንጅ በደንብ ይበቃል» ስትል እየሳቀች ነገረቻቸው፡፡ 
«የሴትና የድስት ትንሽ የለው» ማለቷን ይህንን የሰሙት አባቷም «በሉ እሺታየን አሳውቁልኝ» በማለት መልሳቸውን ገለጹ፡፡ የሠርጉ ቀን ተቆርጦም ጋብቻው ተፈጸመ፡፡ 
መ- የሽታና የሴት ትንሽ የለውም
ንጉሡ ፉራን ታቅፋ ስትመጣ ባዩዋት ጊዜ በጣም ሕፃን ስለነበረች አብረዋት ለማደር አልፈለጉም፡፡ ስለዚህም አብረዋት እንዲያድሩ ዘዴ ማፈላለግ ጀመረች፡፡ በመጨረሻም አንድ ነገር ተገለጠላት፡፡
ንጉሡ ከውጭ ሲመጡ የሆነ ነገር በጣም መጥፎ ነገር  ይሸታቸዋል፣ «ምንድነው?» ብለው ሲጠይቋትም «አይ አንዲት ድመት ነበረች፣ ያች ድመት ትሆናለች» አለችና ትንሽ የድመት ኩስ በእንጨት ጫፍ ይዛ መጣችና እውጭ ጣለችው፡፡
እንደተመለሰችም ንጉሡ በመገረም «የሚደንቅ እኮ ነው ያችን ያህል ትንሽ ነገር የቤቱን ሽታ አናወጠችውኮ፤» አሉ፡፡
«ንጉሥ ሆይ! አዎ¬ን እንደሱ ነው፣ የሽታና የሴት ትንሽ የለውም» ስትል ገለጠችላቸው፡፡ ንጉሡም ምን መልዕክት ለማስተላለፍ እንደፈለገች በመረዳት ከዚያ ዕለት ጀምሮ አብረዋት ማደር ጀመሩ፡፡
ከአራቱ እንቆቅልሾች መልሶች የምንረዳው ፉራ ከሕፃንነቷ ጀምሮ አካባቢዋን በትኩረት የምትከታተልና ብልህ እንደነበረች ነው፡፡
ፉራ በወጣትነቷ አደረገችው እየተባለ በአካባቢው ኅብረተሰብ ከሚነገሩት አፈታሪኮች ውስጥ፣ አንዱ በጣም አመጸኛ ሽፍታ ለብዙ ጀግኖች ወንዶች አልበገር ብሎ ሲኖር የነበረውን ጀግና ከጓደኞቿ ጋር በመሆን ያለ አንዳች የጦር መሣሪያ እንዴት እንዳስወገደችው የሚነገረው ነው፡፡
ሠ- የቆዳ ልብስ ለማስደንበሪያ
በአምስተኛው አፈ ታሪክ መሠረት ፉራ ከዕለታት አንድ ቀን በደንብ ካልለፋ ከቆዳ የተሠራውን ለብሳ ስትሄድ አንድ ነገር ታስተውላለች፡፡ ይኸውም ቆዳውን ቆንጥር ሲነካው ከብቶችና የዱር እንስሳት የሚደነግጡ መሆናቸው ነው፡፡ እንስሳቱ በቀላሉ መደንገጣቸውን ያስተዋለችው ፉራ በቁራጭ እንጨት በደንብ ያልተለፋው ቆዳ በተለያየ ድምፅ ሰጭ ዓመታት መምታት ጀመረች፡፡ ጎጇቸው ውስጥ የነበሩ ሰዎ¬ች ሳይቀሩ ምን መጣብን ብለው ሲወጡ አስተዋለች፡፡ በዚህም መሠረት ጓደኞቿን ታሰባስብና ካልተፋቀ ቆዳ  የተሠራ ቀሚስ እንዲብሱና ጣውላ ይዘው ከሷ ጋር እንዲሄዱ ታደርጋለች፡፡ ከዚያም የታወቀው ሽፍታ ይኖርበታል ወደተባለው ከገደላማ ጫካው ከጓደኞቿ ጋር በድብቅ ትደርስ ሁሉም በያዙት ጣውላ ቀሚሳቸውን በአስፈሪ ሁኔታ በኃይል እንዲመቱ ታደርጋለች፡፡ በዚህ ጊዜ ጫካ ውስጥ ተደብቀው የነበሩት ሽፍቶች ምን መጣብን ብለው ገደል ገብተው ይሞታሉ፡፡

ረ- በአንድ ቀን እወልዳለሁ
ፉራ ወጣት በነበረችበት ጊዜ የነበረው ንጉሥ  «በአንድ ቀን ግንኙነት አርግዛ በአንድ ቀን የምትወልድ ሴት አምጡልኝ» ብሎ ያዛል፡፡ ነገሩ የንጉሥ ትዕዛዝ ነውና ሁሉም ተጨነቀ፡፡ በአካባቢው የነበሩ ኮከብ ቆጣሪ ነን፣ «ብዙ ተአምር እንፈጥራለን» የሚሉ ሰዎ¬ች ሁሉ ከፍተኛ ሽልማት እንደሚሰጣቸው እየተገለጠላቸው በአንድ ቀን አርግዛ በአንድ ቀን የምትወልድ ሴት እንደያገኙ ተለመኑ፡፡ ነገር ግን «ይህችን ለኔ ተዋት፣ እፈጽማታለሁ የሚል ሰው ጠፋ፡፡ ስለሆነም ሰ¬ዎ‹ በተሰጠው ጭራሽ የማይቻል ትዕዛዝ ይጨነቃሉ፡፡ ይህንን ጭንቀታቸውን ወጣቷ ፉራ ትሰማና በጉዳዩ በመጠኑ አሰበችበት፡፡ ወዲያውም «እኔን ዳሩኝ በገባሁ በዕለቱ አርግዠ በዕለቱ ወንድ ልጅ ከነቃጭሉ ዱብ አድርጌለት አድራለሁ» በማለት ታሳውቃለች፡፡ ሽማግሌዎ¬ቹም ትዕዛዙን የምትፈጽም ወጣት መገኘቷን ገልጠው ይድሩለታል፡፡ ከባሏ ጋር እንደተኛችም ማርገዟን ትነግረዋለች፡፡ ወዲያውም ሆድ የሚነፋ መድኃኒት ትጠጣና «ይኸው ሆዴ እየገፋ ነው» ትላለች፡፡ ጥቂት ቆይታም ምጥ ያዘኝ ብላ ያዙኝ ልቀቁኝ ትላለች፡፡ በድሮ ጊዜ ሴቶች ምጥ ሲይዛቸው አንዳንድ አስቸጋሪ ጥያቄ¬ችን ይጠይቁ ስለነበር «ሐዋሳ ሐይቅ ውስጥ አንዲት ያማረች ሚዳቋ ትታየኛለች፡፡ ይህችን ሚዳቋ እስከ ነፍሷ ይዘህልኝ ነገ ጥዋት ብትመጣ ጀግና የጦር መሪ የሚሆን ልጅ እወልድልሃለሁ፡፡ ሀብታምም ትሆናለህ፤» በማለት በምጥ ስሜት እያቃሰተች ነገረችው፡፡ ንጉሡም በአገሩ ባህልና ወግ መሠረት የቀረበለትን ጥያቄ የመመለስ ግዴታ ስለነበረበት ፈረሱን ጭኖ ሌሊቱን ወደ ሐዋሳ ሐይቅ ተጓዘ፡፡ እኩለ ሌሊት ላይም የተባለችውንም የባሕር ሚዳቋ መፈለግ ጀመረ፡፡ ከብዙ ጊዜ አተኩሮ ማየት የተነሳም በሩቁ ሚዳቋ ያየ መሰለውና ወደዚያው ሄደ፡፡ ነገር ግን ሩቅ ስለነበረ ብዙ መጓዝ ነበረበት፡፡ ይልቁንም ቀረብኩ ባለ ቁጥር ሚዳቋ የሚመስለው ነገር ስለሚርቅ ሊደርስበት ከቶ አልቻለም፡፡ ስለሆነም ሚዳቋዋን እደርስባታለሁ ሲል በመድከሙ ለመመለስ ሳይችል ቀረና ሞተ፡፡ እንደሞተም እርሷ ሚስቱ ስለሆነች ነገሠች፡፡
ይህን አፈ ታሪክ የሚሰሙ ምናልባት ተአማኒነት የጎደለው ታሪክ ሊመስላቸው ይችላል፡፡ ነገር ግን የዚያን ጊዜ የነበሩ መሪ¬ዎ‹ አስቸጋሪ የሆነ ጥያቄ የሚጠይቁት ሰው ተጨንቆ ተጠቦ እንዲያስብና ሥራ እንዳይፈታና ወደ ተንኮል እንዳይሄድ ታስቦ የሚደረግ ሊሆን ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የድሮ መሪ¬ዎ‹ ጥያቄያቸው በጥያቄ ሲመለስላቸው የሕይወት መስዋዕትነትም ቢሆን ከፍለው ለመፈጸም ዝግጁ መሆናቸው ነው፡፡ ለምሳሌ በአንድ ቀን አርግዞ በአንድ ቀን የሚወልድ ሰው የሚገባውን ዕርዳታ ባያደርግ ተረቺ ይሆናልና ከሚረታ መስዋዕት ቢሆን ይመርጣል፡፡
እንግዲህ በዚህ ዓይነት ንግሥት ፉራ  ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጥልቀት እያገኘ የመጣ አፈታሪክ ያላት ሴት እንደሆነች እስካሁን የሄድንበት መንገድ ሁሉ ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡ ስለሳባም፣ ስለዮዲትም፣ ስለሌሎችም ሴት መሪ¬ዎቻችን ይህን ያህል ስፋትና ጥልቀት ያለው አፈታሪክ አናገኝም፡፡ «ፉራ ትውልዷ ወደ ሰሜን ቢሆን ኖሮ ገድል ሊጻፍላት ይችል ነበር፤» ያለው የዚህን መጽሐፍ ረቂቅ ያነበበ ጓደኛየ ነገሩን አጋኖ አይቶታል ብየ አላስብም፡፡   
በመጨረሻም ጦረኛነት፣ ነገረ ጥበብ አዋቂነት፣ ወዘተ ሲባል ሌሎች ሰ¬ዎ‹ እንደሚያደርጉት ሁሉ ነው በማለት መተው አግባብ ስላልሆነ የተለያዩ መረጃ¬ዎችን መሠረት በማድረግና የራሴን ዕይታ በመጨመር ልብወለድ ታሪክ አዘጋጅቻለሁ፡፡ 
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜል አድራሻቸው bktesheat@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር