የቡና ባለሥልጣን ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሆን ተጠየቀ

Image result for coffeeየቡናን ዘርፍን በበላይነት እንዲመራ የሚቋቋመው የኢትዮጵያ የቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለሥልጣን፣ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እንዲሆን ጥያቄ ቀረበ፡፡ 
ባለሥልጣኑን ለማቋቋም የተዘጋጀው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ረቂቅ ደንብ እንደሚለው ባለሥልጣኑ ተጠሪነቱ ለግብርና ሚኒስቴር ነው፡፡
ሰሞኑን የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር በረቂቅ ደንቡ ላይ ለመወያየት ባዘጋጀው መድረክ ላይ ቡና ላኪዎች፣ ባለሥልጣኑ ለግብርና ሚኒስቴርም ሆነ ለንግድ ሚኒስቴር ተጠሪ ከሆነ ቀደም ሲል ከነበረው የተሻለ አደረጃጀትም ሆነ ሥልጣን አይኖረውም ብለዋል፡፡
ዘርፉ ያለበት ችግር የተወሳሰበ በመሆኑ ተጠሪነቱ በቀጥታ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እንዲሆን ነጋዴዎቹ አሳስበዋል፡፡
አገሪቱ ትልቁን የውጭ ምንዛሪ የምታገኝበት የቡና ዘርፍ በተለይ ልማቱ በግብርና ሚኒስቴር፣ ግብይቱ ደግሞ በንግድ ሚኒስቴር ሆኖ ቆይቷል፡፡ የቡና ዘርፍ በእነዚህ መዋቅሮች በሚተዳደርበት ወቅት በተከታታይ ዓመታት ከቡና ዘርፍ ትልቅ ገቢ ለማግኘት ቢታቀድም፣ ጠንካራ የማስፈጸም አቅም ያለው የቡና ዘርፍ አመራር ባለመኖሩ ዕቅዱን በስኬት ማጀብ አለመቻሉ ይነገራል፡፡
ይህንን ችግር ለመፍታት የተለያዩ ጥናቶች ከመደረጋቸውም በተጨማሪ፣ ጥናቶቹን ያካሄዱ ኤክስፐርቶች የኮሎምቢያንና የጓቲማላን ልምድ ለመቅሰም የተለያዩ ጉዞዎችን አድርገዋል፡፡ በመጨረሻ የተደረሰበት ውሳኔ በደርግ መንግሥት ዘመን ዘርፉን ሲመራ የነበረውን የቡናና ሻይ ባለሥልጣን መልሶ ማቋቋም ሆኗል፡፡
የቀድሞ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን፣ በአሁኑ ወቅት ለግል ኩባንያዎች የተላለፉት በበቃ፣ ሊሙና ቴፒ  እርሻ ልማት ድርጅቶችን ጨምሮ ያስተዳድር ነበር፡፡
አዲሱ ተቋም የሚያስተዳድረው እርሻ ባይኖርም፣ አገሪቱ የምታመርተውን የቡና ምርት ማሳደግና የተወሳሰበውን የቡና ግብይት ወደ ተሻለ ደረጃ ማሳደግ ይጠበቅበታል፡፡ ረቂቅ ደንቡ በተጨማሪም ሙሉ ሥልጣን ሰጥቶታል፡፡
ላለፉት ዓመታት መንግሥት ከቡና ዘርፍ ብዙ ቢጠበቅም ባለበት ከመሄድ አልፎም ዝቅ ያለ የሥራ አፈጻጸም ሲያስመዘግብ ቆይቷል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከዘርፉ 191 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ ነበር፡፡ ነገር ግን በበጀት ዓመቱ 184 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ተልኮ 780 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል፡፡ ይህ ገቢ ከአምናው በ61 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ ቢኖረውም፣ ዕቅዱ ላይ መድረስ አልቻለም፡፡
የዘርፍ ተዋናዮች እንደሚሉት በቡና የውጭ ገበያ በዓመቱ መጀመርያ ከፍተኛ ችግር የነበረ ሲሆን፣ የበጀት ዓመቱ ሊጠናቀቅ አቅራቢያ የዓለም የቡና ዋጋ ከፍ በማለቱ የተወሰነ ለውጥ መጥቷል፡፡
መንግሥት በቡና ዘርፍ ግብይት በየዓመቱ አሥር በመቶ ዕድገት ለማስመዝገብ ቢያቅድም፣ በተለይ በንግድ ሚኒስቴር ሥር በአንድ አነስተኛ ዲፓርትመንትት የሚመራ በመሆኑ ዕቅዱን መሳካት አለመቻሉ በቡና ላኪዎች ማኅበር ውይይት ላይ ተገልጿል፡፡
ባለሀብቶቹ በማኅበራቸው አማካይነት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር በቅርቡ በጉዳዩ ላይ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ምንጭ፦ ሪፖርተር ጋዜጣ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር