ለዝናብ እጥረት ተጐጂዎች የ230 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ ተጠየቀ

ለዝናብ እጥረት ተጐጂዎች የ230 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ ተጠየቀ-4.5 ሚሊዮን ሕዝብ ዕርዳታ ይፈልጋል
የኢትዮጵያ መንግሥትና ለጋሾች በጋራ በመሆን ባወጡት የሰብዓዊ ድጋፍ ሰነድ፣ በክረምት ዝናብ እጥረት ምክንያት 230 ሚሊዮን ዶላር ሰብዓዊ ዕርዳታ እንደሚያስፈልግ ይፋ አደረጉ፡፡ 
ነሐሴ 18 ቀን 2007 ዓ.ም. የኢትዮጵያ መንግሥት ተወካዮችና ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ድርጅቶች ባወጡት መግለጫ፣ እ.ኤ.አ. በማርች 2015 ወጥቶ የነበረውን የሰብዓዊ ዕርዳታ ሰነድ በመከለስ፣ ቀደም ሲል ተገምቶ ከነበረው በተጨማሪ 1.6 ሚሊዮን ሕዝብ የሰብዓዊ ዕርዳታ እንደሚያስፈልገው ገልጸዋል፡፡ 
የዚህ ምክንያቱም በበልግና በክረምት ወቅቶች በኢትዮጵያ የታየው የዝናብ እጥረት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ቀደም ሲል ሰብዓዊ ዕርዳታ ያስፈልገዋል ተብሎ ተገምቶ ከነበረው 2.9 ሚሊዮን ሕዝብ በተጨማሪ 1.6 ሚሊዮን ሕዝብ የሰብዓዊ ዕርዳታ በመሻቱ፣ አጠቃላይ የተረጂዎች ቁጥርን 4.5 ሚሊዮን እንዳደረሰው የመንግሥትና የሰብዓዊ ድርጅቶቹ የጋራ መግለጫ ያስረዳል፡፡
ለአፋጣኝ የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጐቶች የኢትዮጵያ መንግሥት 700 ሚሊዮን ብር ወይም 33 ሚሊዮን ዶላር መመደቡን መግለጫው ያስረዳል፡፡ 
‹‹የአውሮፓውያኑ 2015 ሲጀምር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ስለበልግ የአየር ሁኔታ ከተነበየው እጅግ የከፋ የዝናብ እጥረት በመከሰቱ፣ የምግብ እህልና የተመጣጠነ ምግብ እህል ችግር ተከስቷል፤›› በማለት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ዕርዳታ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ተጠባባቂ ኃላፊ ዴቪድ ዴል ኮንቴ ገልጸዋል፡፡
በከፍተኛ ደረጃ አምራች የነበሩት የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች በተለይም የአርሲና የምዕራብ አርሲ አካባቢዎች የሰብዓዊ ዕርዳታ እንዳስፈለጋቸው መግለጫው ያብራራል፡፡ 
በአርብቶ አደር አካባቢዎች የተከሰተው የከብቶች መኖና የውኃ እጥረት የከብቶችን ሕይወት እየቀጠፈ መሆኑን መግለጫው ያስረዳል፡፡ 
እ.ኤ.አ. በ2015 መጀመሪያ ላይ የተመጣጣኝ ምግብ አቅርቦት የሚፈልጉ 49 ወረዳዎች በግንቦት ወር ወደ 97 ወረዳዎች ማደጋቸውን፣ በዚህም የተረጂ ሕፃናት ቁጥር ወደ 302,605 ማደጉን ይገልጻል፡፡ 
‹‹በአሁኑ ወቅት ያለው ሁኔታ ቀደም ሲል ባስቀመጥነው ዕቅዳችን ላይ ከፍተኛ ለውጥ ነው ያመጣው፡፡ በመሆኑም የሰብዓዊ ዕርዳታ ተሳትፏችንን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ አለብን፡፡ በመሆኑም በከፍተኛ ደረጃ ያደገውን የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጐት ለማሟላት የለጋሾች ድጋፍ ያስፈልጋል፤›› ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕፃናት አድን ድርጅት (ዩኒሴፍ) ተወካይና የሰብዓዊ ዕርዳታ አስተባባሪ ጁሊያን ሜልሶፕ ተናግረዋል፡፡ 
ነሐሴ 9 ቀን 2007 ዓ.ም. በተፈጠረው የዝናብ እጥረት ላይ መግለጫ ሰጥተው የነበሩት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን፣ በዝናብ እጥረቱ የሚፈጠረውን የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጐት መንግሥት ያለምንም ዕርዳታ እንደሚወጣቸው መናገራቸው ይታወሳል፡፡ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ዕርዳታ እንደማያስፈልግም መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡  
በ1989 እና በ1997 ዓ.ም. በዚሁ የአየር መዛባት ለውጥ በተፈጠረው ድርቅ ኢትዮጵያ በከፍተኛ የዕርዳታ እህል ተጥለቅልቃ እንደነበር የገለጹት አቶ ሬድዋን፣ በበልግ የዝናብ እጥረት የተፈጠረውን የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጐት ማንም ሳይሰማው መንግሥት መመለስ እንደቻለ ተናግረዋል፡፡ በማከልም አሁን በተፈጠረው የክረምት ወቅት የዝናብ እጥረት አስቸኳይ የዕርዳታ ፍላጐት መንግሥት 700 ሚሊዮን ብር መመደቡንና አስፈላጊ ከሆነም እንደሚጨምር ማብራራታቸው ይታወሳል፡፡
የጋራ የሰብዓዊ ዕርዳታ ጥያቄው የመጣው ግን ሚኒስትር ሬድዋን አያስፈልግም ባሉበት ሳምንት መሆኑን መረጃው ያሳያል፡፡   
 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር