‹‹የሐዋሳ ሀብቷ ሆቴሎቿ ናቸው››


አቶ ፍትሕ ወልደሰንበት፣ የሐዋሳ ሆቴሎች ማኅበር ፕሬዚዳንት
 
አቶ ፍትሕ ወልደሰንበት የሐዋሳ ሆቴሎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ የሐዋሳ ሴንትራል ሆቴሎች ሥራ አስኪያጅ ሲሆኑ በማኅበሩ ወቅታዊ እንቅስቃሴ እንዲሁም ቀጣይ ዕርምጃ ታምራት ጌታቸው አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ማኅበሩ እንዴት ተቋቋመ ምን ያህል አባላትስ አሉት?
አቶ ፍትሕ፡- የሐዋሳ ሆቴሎች ማኅበር ከተቋቋመ ገና አንድ ዓመቱ ነው፡፡ መጀመሪያ ፎርም በትነን ሞልተው የላኩና የተመዘገቡ 100 የሚሆኑ ናቸው፡፡ ማኅበሩ አዲስ እንደመሆኑ መጠን ከዚህም በላይ ብዙ አባላት እንደሚኖሩን እንጠብቃለን፡፡
ሪፖርተር፡- አንድ ሆቴል ሲቋቋም ብዙ የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሎ ይታሰባል፡፡ የማኅበሩ አባላት የሆኑ ሆቴሎች በምን ያህል ደረጃ የሥራ ዕድል ፈጥረዋል?
አቶ ፍትሕ፡- ያሰራጨነው ፎርም ብዙ ነገሮችን የያዘ ነው፡፡ ምን ያህል ሠራተኞች አሉ? በምን ያህል ካፒታል ነው የተቋቋመው? ሆቴሉ ምን ያህል የመኝታ ክፍሎች አሉት? የሚሉና ሌሎችም በመጠይቁ ውስጥ የተካተቱ ሲሆን እነዚህን የተሰበሰቡ መረጃዎች ወደ ዳታ ቤዝ ገና እየቀየርናቸው ነው፡፡ ስለዚህ በአሁኑ ወቅት ምን ያህል ሠራተኛ እንደሚያስተዳድሩ መናገር አይቻልም፡፡ ነገር ግን መረጃውን የማጠናቀር ሥራ ሲጠናቀቅ ይታወቃል፡፡
ሪፖርተር፡- የማኅበሩ ተቀዳሚ ዓላማ ምንድነው?
አቶ ፍትሕ፡- አንድ ማኅበር ሁሌም የሚመሠረተው ከችግር በመነሳት ነው፡፡ ችግሩ ካለፈ በኋላ ብዙ የመቀጠል ነገር አይታይም፡፡ እኛ ግን ከዚህ ለየት ያለ ነገር እናስባለን፡፡ ማኅበሩን የመሠረትንበትና ትልቅ ዓላማ ብለን የያዝነው ሐዋሳ ከኢትዮጵያ ተመራጭ የመዝናኛ ቦታ እየሆነች በመሆኑ ከዚህ ገበያ በሰፊው መጠቀም አለብን ብለን ነው፡፡ ወደዚህ ከዓመት ዓመት ሳይቋረጥ ቱሪስቱ እንዲፈስ ከተማችንን የተሻለች ተመራጭ ማድረግ አለብን በሚል ሲሆን ይህ ሥራ ደግሞ በመጀመሪያ ደረጃ የሚጠቅመው ከተማ ውስጥ ያሉትን ሆቴሎች ነው፡፡ ስለዚህ ዋና ትኩረት አድርጐ የተነሳው ከተማዋን የቱሪስት መዳረሻ እንዴት እናድርጋት ከተማችንን እንዴት ተመራጭ ከተማ እናድርጋት የሚለውን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- እርሶም እንደገለጿት ሐዋሳ የአገር ውስጥም የውጭ ሰዎች ለመዝናኛነት የሚመርጧት ከተማ ነች፡፡ እንዲሁም ብዙ ስብሰባዎች የሚካሄዱባት ከተማም ነች፡፡ እነዚህ እንግዶች የሚያርፉባቸው ሆቴሎች ደግሞ ደረጃቸውን የጠበቁ መሆን አለባቸው፡፡ የእናንተ ማኅበር ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጥ ምን እያደረገ ነው?
አቶ ፍትሕ፡- ሐዋሳን ስታስብ ትልቁ መስቧ ሐይቋ ነው፡፡ ከዚያም ሆቴሎቿ ናቸው፡፡ ብዙ ጊዜ አብዛኛው ሰው ጊዜውን የሚያሳልፈው ወይም የሚዝናናው ሆቴሎች ውስጥ ነው፡፡ የሐዋሳ ሀብቷ ሆቴሎቿ ናቸው፡፡ ለግብር ምንጭም የሆቴል ኢንዱስትሪው ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፡፡ ስለዚህ ሐዋሳ ከተማ የቱሪስት መዳረሻነቷ እንዲቀጥልና እንደሌሎች የዓለማችን ምርጥ የመዝናኛ ከተሞች እንድትሆን የሆቴሎች አገልግሎት ደረጃ መጠበቅ የግድ ነው፡፡ ማኅበሩ የተመሠረተበትም ዓላማ ይህንኑ ሥራ ከሥር ከሥር እየተከታተሉ ማሳደግ በመሆኑ በመጀመሪያ ማኅበሩ ያደረገው የሆቴሉን ባለቤትና ሥራ አስኪያጁን ማሠልጠን ነው፡፡ የሆቴል ማኔጅመንት ማለት ምን እንደሆነ ከፍተኛ ግንዛቤ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ እኛ አገር የተለመደው ባለሀብት ሆቴል ይከፍታል ከዛ ባለሙያዎችን ይቀጥራል፡፡ እነሱ ናቸው ሥራውን የሚሠሩት፡፡ ከዚህ በዘለለ ግን የሆቴሉ ባለቤት ሆቴል ከመክፈቱ በፊት ወይ ከከፈተ በኋላ ስለሆቴል አስተዳደር እውቀት ቢኖረው የበለጠ ከባለሙያዎቹ ጋር ተግባብቶ ይሠራል ብለን እናምናለን፡፡ ኢንዱስትሪው በጣም ከፍተኛ ክትትል የሚጠይቅም ነው፡፡ ዝም ብለህ የምትተወው አይደለም፡፡ 24 ሰዓት ያለማቋረጥ በንቃት መሥራትን ይጠይቃል፡፡ ይህን ደግሞ ከማኅበሩ አባላት ጋር የጠበቀ ግንኙነት በመፍጠር ድጋፍ ለመስጠት እየሠራን ይገኛል፡፡ በዚህም በጐ ጅምሮች አሉ እነዚህ ተጠናክረው ይቀጥላሉ፡፡ መንግሥት የሰጠውን የሆቴሎች ደረጃ እንዲጠበቅ ማኅበራችንም ይሠራል፡፡
ሪፖርተር፡- መንግሥት ለሆቴሎች እየሰጠ ስላለው ደረጃ ምን አስተያየት አለዎት?
አቶ ፍትሕ፡- ደረጃ መስጠቱ ዘግይቷል፡፡ ይህም አሁን አሁን እየታየ ያለውን የደረጃ አሰጣጥ ትንሽ ክፍተት እንዲኖረው አድርጓል፡፡ ለምሳሌ አብዛኞቹ ሆቴሎች የተገነቡት በፊት በነበረው የአገሪቱ ነባራዊ እውነታ ነው፡፡ የግንባታ ደረጃው ሌላው ሌላውም ጊዜውን የሚያንፀባርቅ ነው፡፡ የባለሀብቱ ካፒታልም አንድ ወሳኝ ነገር ነው፡፡ በዛው ልክ ደግሞ የሰርቪስ አሰጣጡም እንደዛው የተወሰነ ነበር፡፡ ስለዚህ ደረጃ መስጠቱ ቀድሞ ቢሆን ኖሮ ነገሮችን ከግንባታ ጀምሮ ማስተካከል ይቻል ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- እዚህ ከተማ ምን ያህል አራት፣ ሦስት፣ ሁለት ኮከብ ያገኙ ሆቴሎች አሉ?
አቶ ፍትሕ፡- እንግዲህ ይህ ደረጃ የተሰጠው ጠቅላላ በክልል ደረጃ ነው በክልል ደረጃ ደግሞ ሲሰጥ 18 ሆቴሎች ብቻ ናቸው ደረጃ ውስጥ የገቡት ከእነዚህ ውስጥ 11 ናቸው ሁሉንም አሟልተው የተገኙትና ኮከብ የተሰጣቸው፡፡ በኮከብ ደረጃ አራት ባለአራት ኮከብ፣ ሦስት ባለሦስት ኮከብ የተሰጣቸው ሲኖሩ ከዛ ውጪ ሁለትና አንድ እያለ ይቀጥላል፡፡
ሪፖርተር፡- ይህ የኮከብ ደረጃ አሰጣጥ ተግባራዊ ከሆነ ጀምሮ ብዙ የይገባኛል ጥያቄ እየተነሳበት ይገኛል፡፡ የሪፖርተር ዘጋቢም በሐዋሳ አካባቢ ተዘዋውረን እንደተመለከተው ይህንን ጥያቄ የሚያነሱ በርካታ ናቸው፡፡ ማኅበሩ በጉዳዩ ላይ ምን ይላል?
አቶ ፍትሕ፡- የእኛንም ሆቴል ጨምሮ ቅሬታ አድሮብናል፡፡ ይህን እንግዲህ፣ በድጋሚ ማጥራትና ማየት አስፈላጊ ነው ብለን እናምናለን፡፡ ምክንያቱም ከላይ እንዳልኩት ኮከቡ በትክክል ለሚገባው አካል ካልተሰጠ በከተማዋ ብሎም በክልሉ ዕድገት ትልቅ ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡ ትክክለኛ ሥራ ሠርተው ደረጃ የማይሰጣቸው ከሆነ ነገም ሆቴላቸውን ለማስፋትና ቱሪስቱን የመሳብ ሞራል ነው የሚያጡት፡፡ ክልሉም የኮከብ ሆቴል ባነሰ ቁጥር ተጠቃሚነቱ እየቀነሰ ይመጣልና የኮከቡ ደረጃ አሰጣጥ በጥንቃቄ መታየት አለበት ብለን እናምናለን፡፡ ትክክለኛው ደረጃ ካልተሰጠ ኅብረተሰቡ ኮከቡ ላይ ብዙም እምነት አይኖረውም፡፡ መንግሥት ይህን ደረጃ ሲሰጥ እኛ ደግሞ ሆቴሎቻችንን ማብቃት አለብን፡፡ ሆቴሎቻችን ሲበቁ ቱሪስት ይመጣል፡፡ ቱሪስት ሲመጣ ደግሞ አገሪቷ ትጠቀማለች ማለት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ማኅበሩን እስካሁን ያጋጠመ ችግር ምንድነው?
አቶ ፍትሕ፡- እንደ ማኅበር ስንመሠረት ምንም ችግር አልገጠመንም፡፡ ከከንቲባው ጀምሮ ሙሉ ጊዜያቸውን ሰጥተው ነው የደገፉን፡፡ ከዚህም ባለፈ በጀት በመመደብ ጭምር እየተባበሩን ነው የሚገኙት የተለያዩ ልምድ ልውውጦችን እያዘጋጁ እንድንጠነክር እገዛ እያደረጉልንም ነው፡፡ ትንሽ ችግር ብለን የምንጠቅሰው የአባላት ማነስን ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ብዙ ጥረት የሚጠይቅ ነው፡፡ በክልሉ ውስጥ ያሉ የሆቴል ባለቤቶች አባል እንደሆኑና በሙሉ አባልነት ተመዝግበው ማኅበራችን ተጠናክሮ አንድ ሆነን ብንሠራ ጥሩ ይሆናል ብለን እናምናለን፡፡
ሪፖርተር፡- እንግዲህ ይህ ማኅበር ከገጽታ፣ ከአገር ኢኮኖሚ ግንባታም አንፃር ብዙ ይጠበቅበታል፡፡ ይህን ኃላፊነት እንዴት በብቃት ለመወጣት አቅዷል?
አቶ ፍትሕ፡- እንገደለጽኩት ማኅበራችን ሲቋቋም እንደ ሌሎቹ ችግር ላይ አትኩሮ አይደለም፡፡ ከችግር መፍትሔን አስቀድመን መፍትሔ ማምጣት አለብን፡፡ ከችግሩ በፊት መፍትሔው ከቀደመ ሁሉም ሥራ በአግባቡ ይሠራል ማለት ነው፡፡ የእኛ ሥራ የሆቴል ኢንዱስትሪን አሳድገን የአገር ተጠቃሚነትን ማምጣት ነው፡፡ አንድ ቱሪስት ወደ አገር ውስጥ ሲገባ የመጀመሪያ የሚያገኘው የሆቴል አስተናጋጁን ነው፡፡ እንግዲህ ይህ እንግዳ መጀመሪያ ስለአገሪቷ ያለው እይታ እዚህ ላይ ነው የሚጀምረው ቆይታውም የሚለካው መጀመሪያ ከሚሰጠው አገልግሎት ነው፡፡ እንደ ማኅበር ይህን ጉዳይ ብቻችንን የምንወጣው አይደለም፡፡ ባለድርሻ አካላቱ ሰፊ ስለሆኑ ከሚመለከታቸው ሁሉ ጋር በመሥራት ኢንዱስትሪው ዘመናዊና ታማኝ፣ ጠንካራ እንዲሆን እንሠራለን፡፡ ሌላው አሁን ይህ እየተሰጠ ያለውን የኮከብ ደረጃ ሌላው ዓለም ላይ የሆቴል ማኅበሮች ናቸው የሚሰጡት፡፡ ይህንንም እዚሁ እኛው የምንሰጥበትን ሁኔታ ለመፍጠር ፍላጐቱ አለን ይህንንም የረጅም ጊዜ ዕቅድ በማድረግ እየሠራን እንገኛለን፡፡  

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር