የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ተራዘመ

ሰሞኑን የኣገሪቱ የመገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት በኅዳር 2010 ዓ.ም. ይደረጋል ተብሎ ይጠበቅ የነበረው አራተኛው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ባልታወቀ ምክንያት ተራዝሟል። ዝርዝር ወሬን ከሪፖርተር ጋዜጣ እነሆ፦


በኅዳር 2010 ዓ.ም. ይደረጋል ተብሎ ይጠበቅ የነበረው አራተኛው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ባልታወቀ ምክንያት ተራዘመ፡፡
ለቆጠራው አስፈላጊ የሆኑ የሎጂስቲክ ግብዓቶችና አቅርቦቶች በአብዛኛው ወደ አገር ውስጥ ከገቡ በኋላ ቆጠራው መራዘሙ  ታውቋል፡፡
ከዚህ ቀደም ለቆጠራው ያስፈልጋሉ ተብለው የተገዙ 180 ሺሕ ዲጅታል ታብሌት ኮምፒዩተሮችና 126 ሺሕ ፓወር ባንኮች ግዥ መደነቃቀፎች ገጥሞት የነበረ ቢሆንም፣ አሁን አብዛኛዎቹ ወደ አገር ውስጥ መግባታቸው ታውቋል፡፡
 የግዥ መጓተቱ ለቆጠራው መራዘም ምክንያት ሊሆን ይችላል ቢባልም፣ 665 ሚሊዮን ብር የወጣባቸው ዕቃዎች ግን ባለፈው ሳምንት በአብዛኛው ወደ አገር ውስጥ ገብተዋል፡፡
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 103 መሠረት በየአሥር ዓመቱ መደረግ እንዳለበት የተደነገገው የሕዝብና የቤቶች ቆጠራ፣ ከድንጋጌው በተቃራኒ ለወራት መራዘሙ ታውቋል፡፡
የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ተራዘመ
ከዚህ ቀደም 1999 ዓ.ም. የተደረገው ሦስተኛ የሕዝብና የቤቶች ቆጠራ በሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ መሠረት በ1997 ዓ.ም. መደረግ ቢኖርበትም፣ በጊዜው በነበረው ሦስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ምክንያት ለሁለት ዓመታት እንዲራዘም ተደርጎ ነበር፡፡
አራተኛውን የሕዝብና የቤቶች ቆጠራ መራዘም ቢኖርበት እንኳ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ እንዲደረግ የሚጠበቅ ቢሆንም፣ ይህ ቅድመ ሁኔታ ሳይሟላ እንዲራዘም ማድረግን የሕገ መንግሥት ኤክስፐርቶች ይተቻሉ፡፡
ሦስተኛው ቆጠራ በኅዳር 2000 ዓ.ም. የተደረገ ሲሆን፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 103 መሠረት በአሥረኛ ዓመቱ ኅዳር 2010 ዓ.ም. መደረግ ነበረበት፡፡
የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ዋና ዳሬክተር አቶ ቢራቱ ይገዙ የቆጠራውን መራዘም ያረጋገጡ ሲሆን፣ የመራዘሙን ምክንያት ግን ከመጥቀስ ተቆጥበዋል፡፡
ይህን ጉዳይ በተመለከተ በቅርቡ የሚሰጥ መግለጫ ይኖራል ሲሉ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ሪፖርተር ያናገራቸው ሌላ ኃላፊ ለመራዘሙ የተለያዩ መላምቶችን  አስቀምጠዋል፡፡
‹‹ቆጠራው በዲጂታል ቴክኖሎጂ ታግዞ የሚደረግ በመሆኑ ለዝግጅቱ ሰፋ ያለ ጊዜ ጠይቋል፤›› ያሉት እኝህ ኃላፊ፣ ከዚህ በተጨማሪ ቆጠራው የሕዝብ እንቅስቃሴ በሚረጋጋበት ወቅት ስለሚካሄድ ተመራጭ በመሆኑ ወደ የካቲት መቀየሩ ለዚህ ሳይሆን አይቀርም ብለዋል፡፡
በቅርቡ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች በተፈጠሩ ግጭቶች 75 ሺሕ የሚጠጉ ዜጎች መፈናቀላቸው ይታወሳል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መፈናቀሉ የመቀነስ አዝማሚያ ቢያሳይም ግጭቶቹ ሙሉ በሙሉ ቆመው መረጋጋት የመፍጠር አስፈላጊነት ታሳቢ ሊሆን ይችላል፡፡
የዘንድሮ ቆጠራ 3.1 ቢሊዮን ብር በጀት የተመደበለት ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ 60 በመቶ የሚሆነው ከልማት አጋሮች የተገኘ ነው፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር