የቱሪስት አገልግሎት ጥራት መጓደል ለዘርፉ ዕድገት እንቅፋት መሆኑ ተገለጸ

Image result for Hawassa city  2018
ፎቶ ከክልሉ ቱርዝም ቢሮ

የቱሪስት አገልግሎት ጥራት መጓደል በዘርፉ ዕድገት ላይ እንቅፋት እየሆነ መምጣቱን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ወልደማሪያም ገልፀዋል፡፡
ሀገሪቱ ያላትን የቱሪዝም ሃብት በማልማት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነትን ማሳደግ እንዳልተቻለ የገለጹት ሚኒስትሯ፤ የቱሪስት አገልግሎቶች ጥራት መጓደል ዋነኛ እንቅፋት መሆኑን ተናግረዋል።
"በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን መቅረፍና ቱሪስቶች ለሚከፍሉት ዋጋ ተመጣጣኝ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ወሳኝ ጉዳይ ነው" ብለዋል።
የቱሪዝም ልማት በርካታ ተግዳሮቶች ያሉበት ቢሆንም የቱሪዝም መስህቦችን አልምቶና አስተዋውቆ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሀገሪቱን ተወዳዳሪነትና የዘርፉን ገበያ ለማሳደግ ጥረቱ መጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል።
ለዚህም የአገልግሎት ጥራት ለማሻሻል የሆቴሎች የደረጃ ምደባ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ነው የገለጹት።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከዓለም ቱሪዝም ድርጅት ጋር በመተባበር ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው የሆቴሎች መስፈርት ማውጣቱን አስታውሰዋል።
በዚህም በአምስት ክልሎችና በሁለት የከተማ አስተዳደሮች ለሚገኙ 365 ሆቴሎች የኮከብ ደረጃ መስጠቱን ነው ያነሱት።
በቀጣይም ለቱሪስቶች አገልግሎት የሚሰጡ አዳዲስ ሆቴሎች፣ ሎጆች፣ ሬስቶራንቶችና አስጎብኚ ድርጅቶች የደረጃ ምደባ እንደሚደረግላቸው ጠቁመዋል።
ሀገሪቱ በቱሪዝም ዘርፍ ተወዳዳሪ እንድትሆን ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ያሉ ቸግሮችን መፍታት እንደሚገባም ዶክተር ሒሩት አመልክተዋል።
የደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አክመል አህመድ በበኩላቸው፤ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው በፍጥነት በማደግ ላይ የሚገኝና የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት በኩል ትከረት የተሰጠው ቀዳሚ የኢኮኖሚ ዘርፍ መሆኑን ተናግረዋል።
"ኢንዱስትሪው ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተሰጠው ትኩረት ለውጥ እየታየ ቢመጣም ካለው የቱሪዝም ሀብት አንጻር ለውጡ ዝቅተኛ ነው" ብለዋል።
በቀጣይም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን የሚያረጋግጡ ተግባራትን ማከናወን እንደሚገባ ነው ዶክተር አክመል ያመለከቱት።
እንደ ዶክተር አክመል ገለጻ፣ በደቡብ ክልል 41 ሆቴሎች ተመዝነው 28 ሆቴሎች የኮከብነት ደረጃ ያሟሉ ሲሆን፤ ስምንት ሆቴሎች ደግሞ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ መስፈርቶችን ባለሟሟላታቸው ማረጋገጫ አልተሰጣቸውም።
በአርባ ምንጭ ከተማ የሚገኘው የኢዛና ዓለም አቀፍ ሆቴል ባለቤት አቶ በላይ ሰመረ የሆቴሎች ደረጃ ምደባ የተሻለ አግልግሎት ለመስጠትና የውድድር መንፈስ መፍጠሩን ተናግረዋል።
የቱሪስት አገልግሎቶች ብቃት ማረጋገጥና ደረጃ ምደባ ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ደርበው በበኩላቸው በሁሉም ክልሎች 78 ሆቴሎች የደረጃ ምደባ እንደሚደረግላቸው ጠቁመዋል።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመቀናጀት በሆቴሎች ኮከብ ደረጃ ምደባ ላይ ከዘርፉ ባለሃብቶች ጋር መክሯል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር