ኢትዮጵያ በአይ ኤስ ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ማካሄድ ትችል ይሆን?
( ኤፍ.ቢ.ሲ ) በየማህበራዊ ድረ ገፁ አይ ኤስ በኢትዮጵያዊያን ላይ የፈፀመውን የሽብር ጥቃት አስመልክቶ የተለቀቁ ምስሎችም ሆኑ ፅሁፎች ስር “በቀል እንፈልጋለን”፣ “ወታደራዊ እርምጃ ይወሰድልን” እና የመሳሰሉ አስተያየቶች ይነበባሉ። በእርግጥ ለኢትዮጵያ ወታደራዊ እርምጃ አማራጭ መሆን ይችላል ወይ? አለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታውን በቅርበት የሚከታተሉ ባለሙያዎችስ ስለ ጉዳዩ ምን ይላሉ? የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በፖለቲካል ሳይንስና አለም አቀፍ ግንኙነት፣ ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ ጦርነትና ጦር መሳሪያን በተመለከቱ አለም አቀፍ ስምምነቶች ላይ የሰሩትን ዶክተር ምፅላል ክፍለኢየሱስ በጉዳዩ ላይ አናግረናቸዋል። ባለሙያዋ በመንግስታቱ ድርጅትም 3ኛ ዲግሪያቸውን በሰሩበት ዘርፍ በአማካሪነት ያገለገሉ የወታደራዊ ሳይንስ ባለሙያ ናቸው። አይ ኤስ በዚህ ወቅት ኢትዮጵያውያንን ለማጥቃት ለምን መረጠ? የወታደራዊ ሳይንስ ባለሙያዋ እንደሚያነሱት አይ ኤስ ኢትዮጵያውያን ላይ ይህን ዘግናኝ ድርጊት የፈፀመው በአጋጣሚ አይደለም። ቡድኑ ከመነሻው በቀጣይ ግዛቱን አስፍቶ ስለሚመሰርተው አገር እቅዱን ሲያስቀምጥ ኢትዮጵያ በዚያ ካርታ ውስጥ ትገኛለች፤ አሁን የፈፀመውም ድርጊት ይህን ህልሙን ማሳኪያ አንዱ መንገድ ነው ብለው ያምናሉ። ኢትዮጵያውያንን በእንደዚህ መልኩ ሲገድል አገሪቱ በወሳኝ የፖለቲካ ምእራፍ ላይ መሆኗን ያምናል የሚሉት ዶክተር ምፅላል፥ ከወር በኋላ የሚካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ነው ይህ ታላቅ የፖለቲካ ምእራፍ ይላሉ። እናም ይህ ኢትዮጵያን መዳረሻው ለማድረግ የተነሳ አሸባሪ ቡድን ይህንን ወሳኝ ምእራፍ ተጠቅሞ በቀላሉ የኢትዮጵያውያንን እና የመሪዎቿን አትኩሮት ለመረበሽ ፈልጎ ሊሆን እንደሚችል ትንታኔያቸውን አስቀምጠዋል።