በዘጠኝ ወራት ተገንብቶ የተጠናቀቀው የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የውጭ ኩባንያዎች ሊያስተዳድሩት ነው
ፎቶ ከሪፖርተር ጋዜጣ በታሰበለት ጊዜ መጠናቀቁ ዶ/ር አርከበ ዕቁባይን አስወድሷቸዋል ዘጠኝ ወራት የግንባታ ጊዜ ወስዶ ባለፈው ሳምንት የተመረቀው የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለማስተዳደርና እንቅስቃሴውን በአግባቡ ለማስቀጠል፣ ለህንድና ለቻይና ኩባንያዎች ኮንትራት መሰጠቱ ተገለጸ፡፡ ግንባታውን በታሰበለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ በማስቻልና በጥራት እንዲከናወን በማድረግ፣ በበላይነት በመምራትና በማስተካከል ባደረጉት አስተዋጽኦ ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ ከመንግሥትና ከባለሀብቶች ውዳሴ ጎርፎላቸዋል፡፡ በ250 ሚሊዮን ዶላር በቻይናው ተቋራጭ (ሲሲኢሲሲ) ኩባንያ የተገነባው የኢንዱስትሪ መንደር ዓለም አቀፍ መሥፈርቶች ያሟላና ከብክለት ነፃ የሚያደርግ ቴክኖሎጂ የተገጠመለት ሲሆን፣ በዓመት አንድ ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ እንደሚያስገኝም ተገልጿል፡፡ የፓርኩ አሠራር ውስብስብና ከፍተኛ የማስተዳደር ክህሎት የሚጠይቅና በአገር ውስጥ ባለሙያዎች ለማስተዳደር የሚያስቸግር በመሆኑ፣ በውጭ ኩባንያዎች ለሦስት ዓመታት እንዲተዳደር በመንግሥት መወሰኑን ዶ/ር አርከበ በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ወቅት አስታውቀዋል፡፡ የፓርኩን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴን ጨምሮ አጠቃላይ አስተዳደራዊ ሥራና የጥገና አገልግሎቶችን እንዲያስተዳድር ተቋራጩ ሲሲኢሲሲና የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማስተዳደር ዝና አለው የተባለው ኩን ሻን ኩባንያ በጋራ ኃላፊነቱን ወስደዋል፡፡ እንዲሁም ፓርኩ ከብክለት ነፃ እንዲሆን ፍሳሽ አልባ ቴክኖሎጂ (Zero Liquid Discharge) የተከለው የህንዱ አርቪን ኩባንያ ይህንን ኃላፊነት መውሰዱን ዶ/ር አርከበ ገልጸዋል፡፡ በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ሚኒስትር አቶ ሲሳይ ገመቹ፣ ሦስቱ ኩባንያዎች ፓርኩን ለሦስት ዓመት እንደሚያስተዳድ